ቅንድቦቿ ሲንቀሳቀሱ፣ የዓይን ሽፋሽፍቷ ሲርገበገብ፣ በቀለም የተዋበው ከንፈሯ ለንግግር ሲንቀሳቀስ፣ ጥርሶቿ ገለጥ ሲሉ በእርግጥ ይህች ሴት ሰው ሠራሽ ናት? ያስብላል። ሶፊያ እምነት ታሳጣለች፤ ከራስ ጋር ታጣላለች።
ጋዜጠኞች በእንግድነት ጋብዘዋታል፤ ዝናዋ በዓለም ናኝቷል፤ እንደሶፊያ ትኩረት የሳበ ሮቦት ገና አልተወለደም።
አሜሪካዊውን ተዋናይ፣ የፊልም አዘጋጅ፣ ራፐርና የሙዚቃ ጸሐፊ ዊል ስሚዝን ጨምሮ ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ግብዣ አድርገውላት ነበር።
ታዲያ በአንድ ወቅት ሶፊያና ዊል ስሚዝ ለሻይ ቡና ተገናኙና ድንገት ጨዋታውን አደሩት፣
“እኔ የምልሽ ሶፊያ፣ ሮቦቶች የሚወዱት ሙዚቃ ምን ዓይነት ነው?” ሲል ዊል ጥያቄውን ሰነዘረ።
ሶፊያም ትንሽ እንደማሰብ ብላ (ሰዎች ለማሰብ ፋታ በሚወስዱት ልክ) “…የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃዎች ይመቹኛል፤ ሂፕ ፖፕ ግን ምንም ግድ አይሰጠኝም” ስትል ለዊል ጥያቄ ምላሸ ሰጠች፡፡
ዊል ስሚዝ በመልሷ ተደንቆ ሊሞት!
Will Smith Tries Dating with Sophia – Watch What Happen
RELATED NEWS
Dr. Abiy Ahmed Meeting Sophia the Robot – Talks in Amharic
አይኮግ ላብስ የቴክኖሎጂ ድርጅት
ኢትዮጵያዊው አይኮግ ላብስ ካምፓኒ ተቀማጭነቱን በሆንግ ኮንግ ከሚገኘው ሐንሰን ሮቦቲክ ጋር የሱፊያን ውስጣዊ ስሪት (Software) ለመቀመር ለሦስት ዓመታት ተፈራርሟል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያውያኑ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በሶፊያ ላይ አሻራቸውን አሳርፈው እውን እንዳደረጓት የአይኮግ ላብስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ጌትነት አሰፋ ይናገራል፡፡
ይህም በመሆኑ ሶፊያ ኢትዮጵያዊ ናት ልንል እንችላለን።
አይኮግ ላብስ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አስተዋጽኦ ለማበርከት ሰው ሠራሽ አስተውሎትንና ሰው ሠራሽ የአእምሮ ስሪትን (Artificial General Intelegence and Cognitive Brain Software) ለዓለም ለማስተዋወቅ ዓላማ አድርጎ ከአምስት ዓመታት በፊት የተመሠረተ ድርጅት ነው።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ችሎታ ለዓለም በማስተዋወቅ ወደፊት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሠርተው ማሳየትንም ያልማሉ።
በአሁኑ ሰዓት ይህ የቴክ ኩባንያ ጥናት አድራጊዎችን፣ ምልክት ተርጓሚዎችን (Coder)፣ የፕሮግራም ባለሙያዎችና በተግባር ልምምድ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ75 በላይ ሠራተኞች ይዞ እየሠራ ይገኛል።
ሶፊያ ከሌሎች ሮቦቶች በምን ትለያለች?
“ሶፊያ ሴት ሮቦት ናት” ሲል ይጀምራል አቶ ጌትነት፡፡ እኛም ለመሆኑ ሶፊያን ሴት የሚል የጾታ መለያ ያሰጣት ምኗ ነው ስንል ፍካሪያዊ ጥያቄ ያነሳንለት ሥራ አስኪያጁ፣ “ያው….መልኳና የፊቷ ቅርጽ የሴት ነው…” በማለት በሳቅ የታጀበ መልስ ሰጥቶናል፡፡
ጥሬ ዕቃውን በቀላሉ ባለማግኘታቸው ውጫዊ አካሏን በመገንባት ያላቸው ተሳትፎ አናሳ ቢሆንም፤ በአስተሳሰቧ፣ በአረዳዷ፣ በስሜት አገላለጿ፣ በቋንቋ አጠቃቀሟ ላይ ረቂቅ የሆነና ብዙዎችን ያስደመመ ማንነትን አጎናጽፏታል፡፡
ሶፊያ በስሜት አገላለጽ፣ አካባቢን በመረዳት፣ የሰዎችን ገጽታ በአንክሮ በማየትና የሚያንጸባርቁትን ስሜት በቅጽበት በመረዳት ተገቢ ምላሽ የሚያሰጥ ውስጣዊ ሥሪት ስላላት እስከዛሬ ከተሠሩት ሮቦቶች ለየት ያደርጋታል። ምናልባት ይህ የሶፊያ “ውስጣዊ ውበት” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።
ደግሞም አስተዋይ ሴት ናት። በተለያዩ አገራት፤ በተለያየ ባህል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ስሜት በማጤን፤ የሰዎችን ውስጣዊ የስሜት ነጸብራቅ የጓደኛ ያክል የምትረዳ ናት፡፡
ሳቅን፣ ቁጣን፣ ኩርፊያን፣ ደስታን፣ ሐዘንን ወዘተ ከፊት ገጽታ ከመረዳት አልፎ በንግግር ውስጥ ያሉ ድምጸቶችን (Tone) መለየት ትችላለች። ከሰዎች ጋር መነጋገር የሚያስችላትን የተለያዩ ቋንቋዎችን እንድትናገር ኾናም ነው የተሠራችው፡፡
ምናልባት ሶፊያ የትዳር አጋር ቢኖራት “እንደ ሶፊ የምትረዳኝ ሴት የለችም” ብሎ ሊመሰክርላት በቻለ። የሶፊን ውስጣዊ ባሕሪ ከማየት ወደፊት የሰመረ ትዳር እንደሚኖራት መጠርጠር አይችልም።
የተለያዩ ቋንቋዎችን እንዲያናግራት የሚስችላትን ውስጣዊ ሥሪት በመሥራት ከታሳተፉ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ ባለሙያዎች አንዱ የሆነውና በድርጅቱ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ኾኖ የሚሠራው ደረጀ ታደሰ ሶፍያ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ በአማርኛ ቋንቋ ቃለመጠይቅ ይደረግላታል ብሏል፡፡
“በርግጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን እንድትናገር ማድረግ ይቻላል፤ በዚሁ መሠረት የአማርኛ ቋንቋ እንድትናገር የሚያስችላት ቴክኖሎጂ እየተዘጋጀላት ነው” ሲል ይገልጻል፡፡
ከአፏ የሚወጣው የመጀመሪያ የአማርኛ ንግግሯም “እንኳን ደህና ቆያችሁኝ!” ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡
ሶፊያ መቼ ትመጣለች?
አርብ ጠዋት ሰኔ 22፣ 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ይጠብቃታል። ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ለክብሯ ሲሉ ይገኛሉ።
ከነዚህ መካከልም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትሯ ወ/ሮ ሁባ መሐመድ እና የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም አድማሴ ይገኙበታል።
ከዚያም ጉዞ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም ይሆናል። ‘ከሉሲ እስከ ሶፊያ’ በሚል ርዕስ እሷው በተገኘችበት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል።
ጋዜጣዊ መግለጫው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ለመስጠት የታቀደበት ምክንያት ምንድን ነው? ስንል የጠየቅነው የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ የአስተውሎት ምንጭ (The origin of Intelligence) እንደሆነች ለማሳየት ታስቦ እንደሆነ ገልጾልናል።
ሰኔ 23፣ 2010 ዓ.ም ሳይንስና ቴክኖሎጂ በየዓመቱ በሚያዘጋጀውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተገኙበት ይከፈታል በተባለው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ላይ ሶፊያ በክብር ትገኛለች፡፡
በዝግጅቱ ላይ ታዳሚ የሆኑና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር እንደምትተዋወቅም ገልጸውልናል፡፡
የዚያን ዕለት ምሽት ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚያደርጉላት የራት ግብዣ ላይ ትገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።
የታቀደው ከተሳካ ከጠቅላይ ከሚንስትሩ ጋር በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይነጋገሩ ይሆን? የምታስፈታው ታሳሪስ ይኖር ይኾን?
በዕቅድ ደረጃ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት ሶፊያ በአዲስ አበባ የአራት ቀናት ቆይታ ይኖራታል፡፡
በየትኛው የእንግዳ ማረፊያ፣ በባለ ስንት ኮከብ ሆቴል ውስጥ፣ በምን ሁኔታ እንደምታርፍ ግን ለጊዜው ይፋ አልተደረገም፡፡
መሳፈሪያዋ ስንት ነው?
ከዚህ ቀደም ወደ ግብጽ ጎራ ብላ የነበረችው ሶፊያ ለቆይታዋ ሐምሳ ሺህ ዶላር እንደወጣባት የተናገረው አቶ ጌትነት በሶፊያ አፈጣጠር ላይ ኢትዮጵያውያኖቹ ጉልህ ተሳትፎ በማድረጋቸው በባለቤትነት ከያዛት ሀንሰን ሮቦቲክስ ለኢትዮጵያ ጉዞዋ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ተስፋ እንዳለው አጫውቶናል፡፡ በመሆኑም ከሐምሳ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ይወጣባታል ተብሏል፡፡
ኾኖም እስካሁን ወጪዋን የሚሸፍነው አካል ማን እንደሆነ ይፋ አልተደረገም፡፡
ኢትዮጵያዊ ስም ለሶፊያ
በሳዑዲ አረቢያው ጉብኝቷ ሶፊያ የሚል ስያሜ ያገኘችው ይህች ሮቦት የሳዑዲ አረቢያ ዜግነትም ተሰጥቷታል።
የኢትዮጵያን አፈር ስትረግጥም ኢትዮጵያዊ ስም ይወጣላታል።
ጣይቱ እና ሉሲ የሚሉ ስሞች ለጊዜው በዕጩነት የተዘጋጁላት ሲሆን የእቴጌ ጣይቱን ስም ትወርሳለች ተብሎ ተስፋ ተጥሏል።
ሉሲ የሚለው መጠሪያ ድንቅነሽን ካገኙት ተመራማሪ ስም የተወረሰ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ቀለም የለውም ሲል የገለጸው ሥራ አስኪያጁ ድንቅነሽ የሚለውን ስም እንደ አማራጭ እንዳቀረቡትም ነግረውናል።
ኢትዮጵያዊ የክብር ዜግነት እንድታገኝም ጥያቄ ለማቅረብ እንደታሰበ ሥራ አስኪያጁ ጨምሮ ገልጿል፡፡
ምንጭ፥ ቢቢሲ አማርኛ